በኢትዮጵያ የስነ ተዋልዶ ጤና ውስጥ ካሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ዘላቂ የስነ ተዋልዶ ጤና ስርዓትን ማሰስ
አዲስ አበባ ፡ ኢትዮጵያ ጥር 30 2018 : ዛሬ ለ34ኛ ጊዜ የሚካሄደው እና < በኢትዮጵያ የስነ ተዋልዶ ጤና ውስጥ ካሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ዘላቂ የስነ ተዋልዶ ጤና ስርዓትን ማሰስ > የሚል መሪ ቃልን ያነገበው ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርና በአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ፌዴሬሽን በጋራ የሚዘጋጅ ነው ።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ያለፉትን ሁለት አስርት ኣመታት በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ሰፊ ስራን እየሰራች እና ለውጦችንም እያስመዘገበች የምትገኝ ቢሆንም ከጤናው ዘርፍ ፈጣን እድገት ጋር አብሮ ለመጓዝ የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች መታየታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው ።
የተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ካገቡ ሴቶች መካከል ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶችን የሚጠቀሙ ሴቶች ከ 6.6 በመቶ ወደ 35 በመቶ እድገት አሳይቷል ። የእናቶችና የህጻናት ሞት በከፍተኛ መጠን መቀነስ ተችሏል ፡ የእናቶች ጤና መሻሻሎችን አሳይቷል ፣ የፖሊሲ ለውጦች በመደረጋቸው ምክንያት ደህንነቱ ባልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ ምክንያት የነበረው የሞት ምጣኔ አሳማኝ በሆነ መልኩ ቀንሷል ።
ምንም እንኳ እነዚህ እድገቶች እንደተመዘገቡ ቢነገርም ከዚህ ጎን ለጎንም ፈታኛ ሁኔታዎች መኖራቸው አልቀረም ። ከነዚህ ተግዳሮቶች መካከልም ዋና ዋናዎቹ የስነ ተዋልዶ ጤና መረጃዎች እና አገልግሎቶች አነስተኛ መሆን ፤ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ያሉ ወጣቶች ፣ ያላገቡ ሴቶች ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው እና ሌሎች የተዘነጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ለመድረስ ውሱንነት መኖር እና ባህላዊ እና ማህበረሰባዊ ልማዶች እና በስነ ተዋልዶ ጤና ውጤቶች ላይ ያሉ ልዩነቶች ናቸው ።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዚደንት ዶ/ር ሃይለማርያም ሰኚ < ስለ ስነ ተዋልዶ ጤና ተደራሽነት ስናነሳ እንደኛ ያሉ የሙያ ማህበራት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ ሲሆን በተለይ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ የሆነ ግንኙነት ስላላቸው ከዚህ በፊት ከወሰዱት ሃላፊነት በበለጠ በዚሁ ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ። > ይላሉ ።
< ዛሬ እና ነገ የሚካሄደው ይህ አይነቱ የሙያተኞች መሰባሰብና መወያየትም የተለዩ ክፍተቶችን በአግባቡ በመሰነድና የመፍትሄ አቅጣጫም በማስቀመጥ ከፍተኛ አስተዋጻኦ ሊያደርግ እንደሚችል መረዳት ይገባል ። > ሲሉ አክለዋል ።
የማህበሩ ኤክስኪውቲቨ ዳይሬክተር ዶ/ር አሸብር በበኩላቸው < የጽንስና የማህጸን ማህበር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከሙያ ማህበሩ አባላት ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ለሚገኙ ለተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች በተለይም በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እድገት ታሳቢ ያደረገ የስልጠና እና የማማከር አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል ። > ሲሉ ይገልጻሉ ።
ዶ/ር አሸብር አክለውም <በዚህ አመት እንኳን ከ 70 ለሚበልጡ የሙያ ማህበሩ አባላት የስራ ላይ ስልጠናዎችን ሰጥቷል ፤ ከተለያዩ አጋዥ አጋላት ጋር በመተባበር በተለይም ለእናቶችና ህጻናት ጤና አጋዥ የሆኑ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ለተለያዩ የህክምና ተቋማት ለግሷል ፤ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም በተለይም በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ መረጃዎችን አድርሷል ፤ ከአፍሪካ እና ከአለም አቀፍ አቻ የሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር የሀገራችንን የስነ ተዋልዶ ጤና ሽፋንን ሊያሳድጉ የሚችሉ የእውቀት ሽግግሮችን በማድረግም ሰፊ ድርሻን እየተወጣ ይገኛል ። > ብለዋል ።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እ.አ.አ በ 1992 ዓ.ም የተቋቋመ የሙያ ማህበር ሲሆን ዋነኛ ዓላማውም የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋዥ አካላት ጋር በመሆን በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያግዙ ማስተባበር ነው ።
